Monday, June 15, 2015

የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ውሎ

የዞን 9 ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች ሐምሌ 13 ለብይን ተቀጥረዋል። 1ኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ሲ.ዲ በችሎት እንዳይታይ ታግዷል
በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት የዞን 9 ጦማርያንና ሦስቱ ወዳጅ ጋዜጠኞች ዛሬ ሰኔ 8/2007 ዓ.ም በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡
መዝገቡ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ፍርድ ቤቱ ግንቦት 19/2007 ዓ.ም በነበረው ችሎት ወቅት አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ የሲ.ዲ ማስረጃ አለኝ ባለው መሰረት ፍርድ ቤቱ በጽ/ቤት በኩል ሲ.ዲውን ተቀብዬ አያለሁ ማለቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሲ.ዲውን በጽ/ቤት ተመልክቶ ዛሬ ሲ.ዲው በግልጽ ችሎት ይታይ ወይስ በዝግ ችሎት የሚለውን ይወስናል ተብሎ ሲጠበቅ ጭራሽ ሌሎች ተከሳሾችም ሊመለከቱት እንደማይችሉ የሚገልጽ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በዚህም ፍርድ ቤቱ ‹‹ሲ.ዲውን በችሎት መመልከቱን ተገቢ ሆኖ ባለማግኘቱ….›› በሚል ድፍን ያለ ምክንያት በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ሲ.ዲ ዳኞቹ ብቻ በጽ/ቤት አይተውት እንደ አንድ ማስረጃነት ተቀብሎታል፡፡
ይህን ተከትሎ ተከሳሾች በብይኑ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ ያሰሙ ሲሆን ጠበቆቻቸውም በጉዳዩ ላይ አለን ያሉትን አቤቱታ አስመዝግበዋል፡፡ ጠበቆቹ በአቤቱታቸው እንዳመለከቱት ሲ.ዲው ላይ የጠበቁት ብይን በግልጽ ችሎት ይታይ አይታይ የሚለውን እንጂ ሌሎች ተከሳሾችና ጠበቆቻቸውም እንዳያዩት ይከለከላል የሚል እንዳልነበር ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ክሱ በቡድን በማሴር…በማነሳሳት…›› የሚል ሆኖ ሳለ አንደኛ ተከሳሽ ላይ ቀረበ የተባለውን የሲ.ዲ ማስረጃ ሌሎች ‹‹ግብረ-አበሮች›› እንዳያዩት መከልከል ተገቢ የዳኝነት አሰራር አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ጠበቆቹ በሁለተኛነት በአቤቱታቸው ያስመዘገቡት ሲ.ዲው የቀረበበትን አግባብ በተመለከተ ነው፡፡ አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ በማስረጃ ዝርዝሩ ላይ ያልጠቀሰውን ሲ.ዲ አሁን በማስረጃነት ሲያቀርብ የማስረጃው አይነት የዶክሜንት ነው ወይስ የኤግዚቢት የሚለውንም በግልጽ አላስቀመጠም ብለዋል ጠበቆቹ በአቤቱታቸው፡፡ በተጨማሪም አቃቤ ህግም ሆነ ፍርድ ቤቱ ከአሁን ቀደም በነበረው ችሎት ውሎ አንድ ሲ.ዲ ብቻ እንደቀረበ ሲገልጹ የቆዩ መሆኑን በማስታወስና ተከሳሾችም የተገለጸላቸው አንድ ሲ.ዲ ብቻ ስለመቅረቡ ሆኖ እያለ ዛሬ ፍርድ ቤቱ ብይኑን ሲያሰማ ‹‹ሲ.ዲዎችን ተመልክተናቸዋል›› ማለቱ ግልጽ እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡
ተከሳሾች በጠበቆቻቸው አማካኝነት ያቀረቡትን አቤቱታ ተከትሎ አስተያየቱን የተጠየቀው አቃቤ ህግ በበኩሉ ‹‹ብይን ባገኘ ጉዳይ ላይ አስተያየት አንሰጥም›› በሚል አልፎታል፡፡ ፍርድ ቤቱም ቢሆን አቤቱታው ብይን ባገኘ ጉዳይ ላይ መሆኑን በመጥቀስ ‹‹ይግባኝ ማለት ትችላላችሁ›› በሚል አቤቱታውን ከመመዝገብ ውጭ በአቤቱታው የሚመጣ ለውጥ እንደሌለ አመልክቷል፡፡
በመሆኑም ለአንድ አመት ከሁለት ወር ሲጓተት የዘለቀው የዞን 9 ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች የክስ ሂደት በቀጣይ ቀጠሮ ሐምሌ 13/2007 ዓ.ም ተከሳሾቹ የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ይኖርባቸዋል ወይስ በነጻ ይሰናበቱ የሚለውን ብይን ፍርድ ቤቱ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በእለቱ ችሎቱ ውስጥ ወደ 59 የሚጠጉ የሽብር ክስ ጋር ጉዳያቸው የተያዘ ሰዎች የቀረቡበት በመሆኑ ወላጆች ጋዜጠኞች እና ሌሎች ወዳጆች ችሎቱን ለመታደም አልታደሉም
የዞን 9 ማስታወሻ
እንደተለመደው ፍርድ ቤቱ የጓደኞቻችንን የመከላከል መብት በሚያጠብ መልኩ መወሰኑ የተለመደውን የአቃቤህግን ፍቃድ ብቻ መፈፀሙ እንዲሁም አለአግባብ የተራዘመ ቀጠሮ መስጠቱ በጣም አሳዝኖናል።
ሁልጊዜም እንደምንለው ንፁሃንን ለመፍታት አይዘገይምና ፍርድ ቤቱ ጓደኞቻችን መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲያሰናብት ጥሪ እናስተላልፋለን።
ያልተሰራ ወንጀል ማስረጃ አይገኝለትም።
ስለሚያገባን እንጦምራለን ።
ዞን9

Friday, June 12, 2015

አሸባሪዋ ማሂ

በአለማችን ላይ እንደሰውልጅ በገዛ ፍጡሩ ላይ የሚጨክን አውሬ የለም እስከዛሬ የምንሰማቸው አሰቃቂ እና አስነዋሪ በደሎች አንዱ ሰብአዊ ፍጡር በሌላው ላይ የፈፀማቸው ናቸው፡፡ እንደዚህ ያሉ ክፉ ተግባራት በፍትህ ሽፋን በዚህ ጊዜ በአደባባይ ሲፈፀሙ ማየት ደግሞ እጅጉን ያማል፡፡
ዘመኑን የማይመጥነውና እና የሚያደርገውን ነገር በአግባቡ ማከናወን የተሳነው በመርማሪነት ማዕረግ ማዕከላዊ የሚገኙት ገራፊዎቻችን በማኅሌት ፋንታሁን እና ጓደኞቻችን ላይ ራሳቸው ማስረጃ ማቅረብ ባልቻሉበት ጉዳይ ላይ አስገድደው ‹‹አመፅ ላነሳሳ›› ነበር የሚል  ቃል አንዲሰጡ ሲገደዱ ነበር ፡፡ ማሂም በዚህ “ምርመራ” ሂደት አመፅ አነሳሳች ተብላ አልፋለች፡፡ ከዱላቸው ውጪ አመጽ ተነሳሳ ብለው  ብለው የሚያቀርቡት ፅሁፍ ባይኖራቸውም ዜጎች ተገደው ያላደረግነው አደረግን ካሉ ገራፊዎችን ለመጠየቅ ጉልበትና አቅም የሌለው ፍርድ ቤታችን የፍትህ ስርአቱን  ፍርደ ገምድልነቱን ለማስመስከር ከበቂ በላይ ነው፡፡
እያደር አዲስ የሚሆንብን ወለፈንዲው የአገራችን የኅሊና እስረኞች ጉዳይ ሁሉም ንፅኅናቸውን የሚያረጋግጥላቸው የፍትሕ ሥርዓት ባይኖርም ከተጠረጠሩበት ጊዜ ጀምሮ አሸባሪዎች ናቸው፤ ማስረጃ ባይቀርብባቸውም አንዴ ተብለዋልና ንፁህ ሆነው እያለ ንፁህነታቸውን ማስመክር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አሁን አሁንማ አሰራሩ የማረጋገጥ ሸክሙን ከከሳሽ ላይ አንስቶ ተጠርጣሪዎቸን ንጹህነታችሁን አረጋግጡ ይላል፡፡ ብዙዎች የፍርድ ቤት ክርክርን የሚያደርጉት ፍትሕን እናገኛለን በሚል ሳይሆን የሚደረገውን ድርጊት ሕዝብ እንዲያውቀው ሥርዓቱን ሁሉም እንዲረዳው ፤ ምናልባት የተጠራጠሩዋቸው ካሉ አንዲያውቁት እድል ለመፍጠርና ይህ እንደማይገባን ለማሳየት አጋጣሚውን መጠቀማቸው ነው፤ እንጂማ በግፍ እንደሚፈረድባቸው እያወቁ  ፍርድ ቤቱንም ሆነ አሰራሩን እውቅና መስጠት አምሯቸው አይደለም፡፡ ትሁቱ ናትኤል ፈለቀ እንዳለው እያደረጉ ያሉት “Judicial activism” ነው፡፡
የምርመራ ሂደቱ ደጋግመው ቢወሩ አንደአዲስ የሚያስገርሙ ብዙ ጉዶች አሉት ፡፡ ጥፋት አለብህ ብሎ ያሰረህ መርማሪ ‹‹ጥፋቴ ምንድን ነው ትላለህ?›› ብሎ ይጠይቅሃል፡፡ ‹‹ሕገ-መንግስቱ ተከብሮ እያለ ሕገ-መንግስቱ ይከበር በማለቴ ጥፋተኛ ነኝ›› በል ብሎ ፍዳህን ያበላህ መርማሪ መልሶ ቢሮ አስጠርቶህ ስለሕግ አስጠናኝ የቤት ሥራም ሥራልኝ ይልሃል አንተን ‹‹አሸባሪውን››
ከፃፍነው፣ ስንጦምረው ከኖርነው ውጪ ሌላ አላማ ካላገኘንባችሁ ያሉ ገራፊዎቻችን ‹‹አላማችሁ ምንድነው?›› በተደጋጋሚ የሚያነሱት 24 ሰአት ሙሉ የሚደጋገም ጥያቄያቸው ነበር፡፡  ያላለቀው ግን ያለፈውን ምርመራ ዛሬ ላይ ማሂ ስትቀልድበት እንዲህ የምትል ይመስለኛል
አላማችሁ ምን ነበር?
ዓላማችን
·         የማዕከላዊ ምርመራን በመጎብኘት የምርመራ ሂደቱን ምጡቅነት እና ዘመናዊነት መታዘብ፡፡
·         ክስ ሲመሰረት እንዴት በተልከሰከሰ መልኩ እንደሆነ ለዓለም ማሳየት፡፡
·         አቃቤ ሕግ እና መርማሪ እንዲሁም ዳኛ የጆሮ ጉትቻ እና የአንገት ሃብል መሆናቸውን ማሳየት፡፡
·         የሽበር አዋጁ እንዴት abuse እንደሚደረግ በተግባር ማረጋገጥ (አንድ ሰው ከሱቅ ዳቦ ሲገዛ ቢገኝ ዳቦውን በልተህ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ልታስብ ስለነበር ተብሎ የፀረ ሽብር አዋጁ ተጠቅሶ መከሰሰስ እንደሚችል ማሳየት እና ለዚህ ዋናው እና አስፈላጊው ነገር የመንግስት ለመክሰስ የማሰብ ፍላጎት መኖር  ብቻውን በቂ መሆኑን ማሳየት ነው)
ግባችን ደግሞ፡- የፍትሕ ሚኒስቴር እንጂ ፍትሕ እንደሌለ ማሳየት ነው፡፡
 አሸባሪዋ ማሂ
በተለያየ አጋጣሚ ሰዎች በራሳቸው ጥፋት ሲቀየሙን አልያም ሲያኮርፉን “ጥፋቱ የእኔ ይሆን?” ከሚል በተለየ አንግል ለማየት እና ለመረዳት ብዙዎቻችን ሞክረን እናውቃለን፤ በአገራችን ሃሳብን በነፃነት መግለፅ መንግስትን እንደ መዳፈር፣ መብትን መጠየቅ አሸባሪ የሚል ካባ የሚያስደርብ ኖርም ከሆነ ሰነባብቷል፤ ብዙዎች ሃሳብህን በመግለፅህ የሚደርስብንን ነገር በመስጋት ያንን ስጋት የፈጠረውን ስርዓት ከመታገል ይልቅ የአቅማቸውን የሚሞክሩትን ማስፈራራት የእለት ተዕለት ተግባራችን ሆኗል፡፡
ይህ በአንባገነን ሥርዓት ውስጥ ዜጎች ላይ የተጫነው የፍርሃት ቀንበር ራስን ከማስገዛት አልፎ ሌሎችንም ዝም ለማሰኘት እርስ በርሳችን የሸበበን የማይገባንን ሥርዓት ተሸክምን ያለአግባብ ዜጎች ላይ በደል ሲደርስ ለምን ብለን ከመጠየቅ ይልቅ ‹‹አርፈው አይቀመጡም ነበር›› የሚል በጭለማ ውስጥ ያለ የውሸት እውነት ነው፡፡
ማሂን በዞን ዘጠኝ በነበረን ጓደኝነት የራስዋ አበርክቶ ያላት ለብዙ እንስቶቻችን ምሳሌ መሆን የምትችል ብሩህ ወጣት ናት ማሂን እኔ ሳውቃት ስልክ ደውላ አዲስ መፅሃፍ ወጥቷል ናና ሸማምት፣ የመፅሃፍት ምረቃ አለ ለምን አትመጣም፤ እና ሌሎች ይህን መሰል አስተያየቶችን ነበር የምትነግረኝ ፡። የስነጽሁፍ ፍቅሯንም ከራሷ አልፎ ለእኔም ታጋራ ነበር፡፡
ስርአቱ ስርኣት አልባ ነው፣ ዜጎችን ለማሸማቀቅ በዝምታ እንዲገዙ ለማድረግ የሚታትረው ስርኣት የሚሸማቀቁ እና ዝምታን የሚመርጡ እንደሚኖሩ ሁሉ የሕግ የበላይነት የሚባል ነገር እንደሌለ የሚታያቸው ስርዓቱን ለመሞገት ዴሞክራሲያዊ መንገድ አማራጭ እንደማይሆን የሚገለጥላቸው ብዙ ዜጎችም መፈጠራቸውም ሊስቱት አይገባም፤ ሥርዓት አልበኛውን ስርዓት መካሪ የለውም በዘር እና በጥቅማጥቅም እና የፕሮፓጋንዳ ሰለባ ሆነው የተያዙትም የስርኣቱን ስርዓት አልበኝነት እና ሕገ-ወጥነትን ጀስቲፋይ ሊያደርጉት ይዳዳቸዋል፡፡
የማይቻላቸውን ለቻልሽው ማሂ ይህ የማያልፍ የሚመስለው ክፉ ቀን ቶሎ እንዲያልፍ ምኞቴ ነው፤ በሰፊው እስርቤትም እስክንገናኝ እናፍቃለሁ፡፡


መልካም ልደት እንኳንም ተወለድሽ፡፡   

Tuesday, June 2, 2015

ፍርድ ቤቱ በአቤል ዋበላ ላይ የ4 ወር የእስር ቅጣት በ2 አመት ገደብ ወሰነ

በእነ ሶልያና ሽመልስ የክስ መዝገብ 7ኛ ተከሳሽ የሆነው ጦማሪ አቤል ዋበላ ዛሬ ግንቦት 25/2007 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ብቻውን ቀርቧል፡፡ አቤል ግንቦት 19/2007 ዓ.ም የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች በነበራቸው የፍርድ ቤት ውሎ ወቅት ‹‹ችሎት ደፍረሃል›› በሚል ጥፋተኛ ያደረገው ፍርድ ቤቱ ዛሬ የቅጣት ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚህ መሰረት ፍርድ ቤቱ በአቤል ላይ የ4 ወር የእስር ቅጣት የበየነ ሲሆን፣ አቤል ድርጊቱን የፈጸመው በስሜታዊነት መሆኑን በመገንዘብ ቅጣቱ በ2 አመት ገደብ እንዲወሰን በማድረግ ማቅለሉን ፍርድ ቤቱ በብይኑ ላይ አመልክቷል፡፡ ጦማሪ አቤል ባለፈው የፍርድ ቤት ውሎ ወቅት ጥያቄ ለማንሳት እድል እንዲሰጠው ሲጠይቅ ‹‹ስነ-ስርዓት አድርግ!›› በሚል ኃይለ ቃል ፍርድ ቤቱ ሲናገረውና ሀሳቡን እንዳይገልጽ ሲገድበው፣ ዳኞችን ‹‹እናንተ ራሳችሁ ስነ-ስርዓት አድርጉ!›› በማለቱ ችሎት ደፍረሃል መባሉ ይታወሳል፡፡

ሌሎች የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ወዳጅ ጋዜጠኞች ፍርድ ቤት ውስጥ በአቤል ላይ የጥፋተኛነት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ የእሱ ሃሳብ እኛንም የሚመለከት ስለሆነ ቅጣቱን አብረን እንቀበላለን፤ ስለሆነም በቅጣት ውሳኔው ዕለት እኛም ፍርድ ቤት እንድንቀርብ ይታዘዝልን ብለው የነበር ቢሆንም በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ሳያቀርቧቸው ቀርተዋል፡፡ አቤል ከጓደኞቹ ተለይቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻውን ችሎት ፊት የቀረበ ሲሆን፣ ፍጹም ልበ-ሙሉነትና ዘና ያለ ስሜት ታይቶበታል፡፡

ጦማሪ አቤል በቅጣት ውሳኔው ላይ ምንም ሀሳብ አልሰጠም፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ‹‹እስካሁን እንደነበረው አካሄድ ከስሜታዊነት በወጣ መልኩ ወደፊት ችሎቱን ተከታተል›› የሚል ‹ምክረ ሀሳብ› አቅርቦለታል፡፡

ችሎቱን የአቤል ቤተሰቦች፣ ወዳጆቹ፣ ጋዜጠኞችና ከአሜሪካና ጀርመን ኤምባሲዎች የመጡ ተወካዮች ተከታትለውታል፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማርያንና ሶስቱ ወዳጅ ጋዜጠኞች በቀጣይ ሰኔ 8/2007 ዓ.ም ለ30ኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ በአንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ አቃቤ ህግ አቅርቤዋለሁ ባለው የዶክሜንተሪ ማስረጃ ላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተያያዘ ዜና ምክንያቱ በግልጽ ባልታወቀ ሁኔታ በቅሊንጦ ታስረው በሚገኙ የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች ዞን ላይ ለውጥ የተደረገ ሲሆን ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ እና ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ ወደ ተለያዬ ዞኖች ተዘዋውረዋል፡፡

በዚህም መሰረት
በዞን1 ጦማሪ ዘላለም ክብረት ፣ ጦማሪ አቤል ዋበላ እና ጦማሪ ናትናኤል ፈለቀ
በዞን2 ጦማሪ በፍቃዱ ሃይሉ ፣ ጦማሪ አጥናፍ ብርሃኔ እና ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ
በዞን3 ጋዜጠኛ አስማማው ሃይለጊዮርጊስ ይገኛሉ ፡፡

ስለሚያገባን እንጦምራለን !
ዞን9

Saturday, May 30, 2015

ሥነ-ስርዓት! የአቤል ማስታወሻ ከቅሊንጦ

“they say that time heals all things,they say you can always forget;
but the smiles and the tears across the years
they twist my heart strings yet!”
― George Orwell1984
የመታሰሬ ምክንያት መናገሬ ነው ፡፡ መንግሰት በሬ ወለደ “ሽብር” የሚል ክስ ሳይመስርትብኝ በፊት ይጠይቀኝ የነበረው በማህበረሰብ ሚዲያ የምጽፍበትን የምናገርበት አላማ ነበር፡፡ አላማዬ ተፈጥሮአዊ የመናገር መብቴን ማከናወን አንደሆነ ስናገር ከዚህ ተጨማሪ ሌላ ምክንያት ያለኝ ይመስል የተረፈኝ ድብደባ ነበር ፡፡ በዚህ ሂደት ወትሮም ገመምተኛ የነበረውን ግራ ጆሮዬን አጥቻለሁ፡፡ የሚቆጨኝ ነገር የለም፡፡ የሚያስቆጭ ነገር ካለም መቆጨት ያለብኝ የመናገር ነጻነት ያለውና ያን ነጻነቱን የሚጠቀም ሰው ሆኜ በመፈጠሬ ነው ፡፡

አላማዬ መናገር ነው ፡፡ አላማዬ መማር መማማር፣ ግድየለሽነትን በእውቀት ማስወገድ ነው ፡፡ ይህ አላማዬ ከማንም ያልተቀበልኩት ሰው በመሆኔ ብቻ ያገኘሁት ነው፡፡ ይህንን መሰረታዊ የሰውነት መብቴን ማንም አንዲነፍገው አልፈቅድለትም ፡፡ የመንግሰት ሹመኛ ይሁን ተራ ግለሰብ ፣ ተቋም ይሁን ማህበረሰብ የመናገር መብቴን ልሰጠው አልደራደርም ፡፡
የምናገረው በአደባባይ ፣ በገዛ ቤቴ ፣ በማህበራዊ ሚዲያ በእስር ቤት በፍርድ ቤት በፓሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል በአጠቃላይ በአካባቢዬ ያለውን ግለሰብና ቡድን ሳላውክ በሃላፊነት ነገር ግን በማንኛውም ቦታ ነው ፡፡ ይህንን እነዳላደርግ ቁጣ ፣ ማስፈራሪያ፣ የማሰቃየት ተግባር እስርና ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ  መብቶች መከልከል አላገደኝም ለወደፊትም እንዲያግደኝ አይሆንም ፡፡
ጓደኞቼም ሆነ እኔ አሁን ያለንበትን እስር ማስወገድ እንድንችል ስደትና ሌሎች መንገዶች አንድንመለከት ሥርዓቱ በደህንነት ሰራተኞቹ ጥቆማ ሰጥቶን ነበር፡፡ የመጨረሻዋ ሰአት ስትቃረብ ከልብ የሆነ አእምሮን የሚፈታተን ውይይት አድርገን ነበር፡፡ ከመታሰራችን ቀናት ቀድሞ ሚያዝያ 15/2006 በገጻችን ዞን9 አንዳስነበብነው“ ተፈጥሮአዊና ህገ መንግሰታዊ መብታችንን ማስረከብ “ እጅግ ስለበዛብን የምንከፍለውን ዋጋ እና የስርአቱን ቂመኝነት እያወቅን መናገራችንን አንደምንቀጥል አውስተን ነበር፡፡

የተራዘመው የእስር ጊዜም ይሄንን አቋም አልለወጠውም፡፡ አሁንም መናገር አሁንም ሃሳቤን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ይህ ሰው ሆኖ የመወለድ መብት በምንም አይነት ላባክነው አልፈልግም፡፡ግንቦት 19/2007  በዋለው ችሎትም የተፈጸመውም ይሄ ነው፡፡ 

ይህንን ክስ የሚከታተል ሰው ሁሉ አንደሚያውቀው19ኛ ወንጀል ችሎት በቀረብንባቸው ጊዜያት ዳኞቹ ንጽህናችንን የምናረጋግጥበትን እድል የሚያጣብቡ ውሳኔዎቸን መወሰናቸው ፣ የራሳቸውን ውሳኔ መልሰው መካዳቸው ፣ አቃቤ ህግ በቸልተኝነት የፍትህ ሂደቱን አንዲያዘገይ መፍቀዳቸው ፣ ማረሚያ ቤት የሚደርሱብንን የመብት ረገጣዎች ሰምተው አጥጋቢ እርምጃ አለመውሰዳቸው ሳያንስ ከሁሉም የከፋው ደሞ ችሎት ውስጥ እነዳንናገርና ሃሳባችንን እንዳንገልጽ ማፈናቸው ነው ፡፡

ይህንን ተከትሎ መፍትሄ ይሆናል በማለት ሃሳባችንን በችሎት እንዳንገልጽ መታፈናችንን በመግለጽ የመሃል ዳኛው አንዲቀየሩ አቤቱታም አቅርበን ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ጥያቄያችንን ውድቅ ቢያደርገውም መሃል ዳኛው በራሳቸው ፍቃድ ከእኛ ( ከነሶልያና ሽመልስ) የክስ መዝገብ ራሳቸው አግልያለው ብለው የነበረ ቢሆንም አሁንም ድረስ የሚሰየሙት ራሳቸው ናቸው :: ችሎቱም አንደተለመደው ለአቃቤ ህግ እንደፈቀደ ለእኛም ሆነ ለዳኞቹ ለራሳቸው የማይገቡ ነገሮች የሚናገርበት እኛም አንዳንዴ ካልሆነ በስተቀር እንዳንናገር የምንታፈንበት ሆኖ በኤሊ ፍጥነት እያዘገመ ነው ፡፡

ይህ መዘግየት አንደሚያሳስበን ዳኞቹ የተረዱ አይመስለኝም፡፡ በነጻነት ልናደርጋቸው የምንፈልጋቸው ነገሮች አንዳሉን ከሚወዱንና ከምንወዳቸው ሰዎች እስር ቤቱ አንደነጠለን ዘንግተውታል፡፡
የአገሪትዋን የማረሚያ ቤቶች ሁኔታ እና የማረሚያቤቶቹን የእስረኞች አያያዝ አያውቁት ይመስል፣ እኛ የተፈጠርንበትን የጉድ ዘመንና የምንተውንበት ወለፈንድ ድራማ አስገርሞን ፈገግ ማለታችንን አይተው እስሩ የተመቸን እየመሰላቸው በቀጠሮ ላይ ቀጠሮ መደራረባቸው አግባብ አለመሆኑን መናገር ነበረብኝ ፡፡ መታሰራችን ጤናማ መንፈሳችንን እያደከመ መሆኑን አቃቤ ህግ እስከዛሬ አለኝ ሲል ያልተደመጠውን በድንገት ያመጣውን አንድ ዶክመንተሪ ሲዲ (አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ የቀረበ) ለማየት ሃያ ቀናት መውሰዱ ፣ በአጭር ቀናት ውስጥ አይተው በፍጥነት ወደቀጣዩ የፍርድሂደት እንድንሄድ አንዲደርጉ ለመግለጽ በፍርድ ቤቱ ሥርአት መሰረት እጄን አውጥቼ አውጥቼ አሳየሁ። አንደተለመደው እነዳንናገር ዳኞቹ እቀባ በማድረግ የመሰማት እድላችንን ነፈጉን ፡፡ ለመናገር ፍቃድ ስንከለከል ሳይፈቀድልን መናገር ጀመርን ፡፡ “ የምጣዱ ሳለ የእንቅቡ ተንጣጣ” አንዲል ያገሬ ሰው ተበድለን በተናገርን “ስነስርአት አድርጉ” የሚል ትእዛዝ ከዳኞቹ መጣ፡፡ በዚህ ሰአት “እናንተ ራሳችሁ ሥነ-ስርዓት አድረጉ” በማለት ስርአት አልበኛ የሆነው የንጹሃን ዜጎችን መብት ለማፈን የተዘጋጁት እነሱ መሆናቸውን ተናግሬያለሁ፡፡ ይህንን ስናገር ስሜት ተጭኖኝ ይሆናል፡፡ ነገር ግን በዚያ ችሎት የሚፈጸመውን በደል ትውልድ እንዲረዳው ታሪክም መዝግቦ አንዲያቆየው መዘከር ነበረብኝ፡፡
ጦማሪ አቤል ዋበላ

ሥነስርዓት ምን እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ወላጆቼ በገባቸው መጠን ጥብቅ በሆነ ስነስርዓት አሳድገውኛል፡፡ ይህ ታላቅን ብቻ ሳይሆን ታናሽንም ማክበር አንደሚገባ ሥነ-ስርዓትና ደንቦችን መጣስ አንደማይገባ ይጨምራል፡፡ ( በሁለት አመት የዞን9ሥራቸንም ለማንኛውም የአገሪቷንህግ ሳንጥስ ህጋዊ ሆነን የቆየነው ለዚያምጭምር ነው ) ነገር ግን መታፈንን በጻጋ መቀበልና በደልን መሸከምን አይጨምርም፡፡ የማንም ሰብአዊ መብት ተሟጋች ወይም ነጸ አውጪአይደለሁም ፡፡ የግለሰብ መብቴ ሲነካ ግን ዝም ማለት አልወድም ፡፡ በተለይም ደግሞ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብቴ አንዲከለከልአልፈልግም ፡፡ ስለዚህም ይህንነ ከዚህ በፌት ላደረገ ፣ ከአሁን በማድረግ ላይ ያለ ፣ ወደፌትም ለማድረግ የሚያስብን ሁሉ አስጠነቅቃለሁ………….ሥነ-ስርዓት !!

Thursday, May 28, 2015

የጦማርያኑ እና የጋዜጠኞቹ የሃያ ዘጠነኛ የፍርድ ቤት ውሎ

ከትላንትና ወዲያ በምሰክሮች እና ሲዲ ውዝግብ በይደር ተቀጥሮ የነበረው የነሶልያና ሽመልስ የክስ መዝግብ የፍርድ ቤት ውሎ ትላንትናም በተለያዬ ድራማዎች ታጅቦ ለግንቦት 25 እና ለሰኔ 8 ተቀጥሯል፡፡
የፍርድ ቤቱ ብይን
ፍርድ ቤቱ በ29ኛ ቀጠሮው ተጨማሪ ምስክሮችን ለመስማት እና ሲዲ ማስረጃዎች ላይ ብይን ለመስጠት የነበረ ሲሆን በዚህም መሰረት
1. የሲዲ ማስረጃ ተብለው አቃቤ ህግ በተደጋጋሚ የሚያነሳቸው ነገር ግን በስተመጨረሻ ከኮምፒውተር ላይ የሰነድ ማስረጃዎቸን ለመገልበጥ ብቻ የተጠቀምኩባቸው ናቸው ያላቸውን ሲዲዎች የኤግዚቢትም የሰነድም ማስረጃ ስላልሆኑ ሙሉ ለሙሉ አንዲሰረዙ ሲል ፍርድ ቤቱ ወስኗል፡፡ አቃቤ ህግ ከመጀመሪያው የማስረጃ መስማት ሂደት አንስቶ እስከ 28ተኛው ቀጠሮ ድረስ አንዴ ባለሞያዎች የሉም ሌላ ጊዜ የወንጀሉ ኤግዚቢት ናቸው ሲላቸው የከረሙትን ሲዲዎች በስተመጨረሻ ምንም አይነት የተለየ ይዘት ያላቸው ሲዲዎች የሉኝም ሲል አምኗል፡፡ እነዚህ ሲዲዎችን አስመልክቶ ብቻ ትንሽ የማይባሉ ቀጠሮዎች መሰጠታቸው ከዚያም በተጨማሪ የጦማርያኑ እና የጋዜጠኞቹ እነዲሁም የጠበቆች እና የፍርድ ቤቱ ጊዜ እና ጉልበት መባከኑ ይታወቃል፡፡
2. አቃቤ ህግ የጠየቀውን ተጨማሪ ምስክሮች ተፈልገው አንዲመጡ ጊዜ ይሰጠኝ ያለውን ጥያቄ አስመልክቶ ምስክሮቹ አሁንም የደረጃ ምስክሮች በመሆናቸው እቃ ሲፈተሽ አይተናል ከማለት ውጪ ስለማይመሰክሩ አቃቤ ህግም በተደጋጋሚ በፍርድ ቤቱ እድል ተሰጥቶት ምንም የተለየ ምስክር ሊያቀርብ ባለመቻሉ ተጨማሪ ምስክሮችን ለማቅረብ ተጨማሪ ቀጠሮ አይሰጠውም በማለት የምስክሮቹን ጉዳይ ፍርድ ቤቱ ዘግቶታል፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስን የተመለከተ ማስረጃ
አቃቤ ህግ እስካሁን ምንም ሳይል የቆየባት አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስን በተመለከተ በትናንትናው የፍርድ ቤት ውሎ ማጠቃለያ ላይ አንድ ዶክሜንተሪ የያዘ ሲ.ዲ በማስረጃነት ማቅረቡን ገልጾ ፍርድ ቤቱ እንዲመለከተው ማመልከቱ ይታወሳል፡፡ ይህን የሲ.ዲ ማስረጃ በተመለከተ በ29ኛው ችሎት ቀጠሮ ብይን የተሰጠ ሲሆን፣ በብይኑ መሰረትም ትላንትና ከሰዓት በኋላ አቃቤ ህግ ሲ.ዲውን በጽ/ቤት በኩል እንዲያስገባ ታዝዟል፡፡ ፍርድ ቤቱ ጨምሮ እንደገለጸው በአንደኛ ተከሳሽ ላይ የቀረበውን ዶክሜንተሪ በቢሮ ዳኞቹ እንዲመለከቱት ከተደረገ በኋላ ሲ.ዲው ሌሎችን ተከሳሾች ይመለከታል ወይስ አይመለከትም የሚለውን አይቶ ብይን የሚሰጥ ይሆናል፤ ብይኑን ለመስጠትም ለሰኔ 8/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም ሲ.ዲው የያዘው ዶክሜንተሪ በግልጽ ቢታይ የሚያስከትለው ጉዳት አለ ወይስ የለም የሚለውንም ፍርድ ቤቱ ብይን እንደሚሰጥበት ይጠበቃል፡፡ አቃቤ ህግ በቀደመው ችሎት አንደኛ ተከሳሽ አመጽ ስታነሳሳ የሚያሳይ ዶክመንተሪ ሲዲ አለኝ ማለቱ ይታወሳል፡፡
አቃቤ ሀግ ጠበቆች ላይ ያቀረበው አቤቱታ
አቃቤ ህግ በዚሁ ችሎት ጠበቆች የፍርድ ቤቱን ውሎ አስመልክቶ የሚሰጡትን አስተያየት የአንድ ወገን አስተያት ከመሆኑም በላይ የፍርድ ሂደቱን ተጽእኖ ሊያመጣ ይችላል የሚል በቤቱታ አቅርቧል፡፡
ጠበቃ አምሃ መኮንን በበኩላቸው አቃቤ ሀግ እዚህ አንድ ተከራካሪ ወገን አንጂ የሂደቱ አዛዥ አለመሆኑን በተጨማሪም ግድፈት ካለ የተጣሰውን ህግ ግድፈት በጽሁፍ አቤቱታ ማቅረብ አንደሚችል ከዚያ ውጪ ግን በግልጽ የተሰየመውን ችሎት ከአገር ቤት እስከአለም አቀፍ ሚዲያዎች በዝርዝር አንደሚዘግቡትና የጠበቃው አስተያየትም ከዚህ የተለየ አንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ ‹‹የተሰጠው አስተያየት አቃቤ ህግ በሰጠው ቃል መሰረት ተፈጽሞ ከሆነ ስህተት ስለሆነ ሊስተካከል ይገባል›› በሚል ማሳሰቢያ ብቻ አልፎታል፡፡
በፍርድ ቤትም ውስጥ የታፈነው የተከሳሾቹ ድምጽ
ብይኑ መሰማት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በተደጋጋሚ ጥያቄ ለመጠየቅ ሲጠይቁ የነበሩት ተከሳሾች በፍርድ ቤቱ እድል አልተጣቸውም ፡፡ በተለይም የአቶ አመሃን የሚዲያ አስተያት ተከትሎ
ጦማሪ ናትናኤል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር በተከሳሾች ላይ የወንጀለኛነት ንግግር ሲያደርጉ መደመጣቸውን በማስታወስ የፍርድ ቤቱ ማሳሰቢያ ለእሳቸውም ይሁን በማለት ንግግሩን ለማብራራት ሲሞክር ፍርድ ቤቱ ‹‹ይሄ የአቶ አምሃ ጉዳይ እንጂ እናንተን አያገባችሁም›› በሚል አቋርጦታል፡፡ ጦማሪ ዘላለም ክብረትም አንዲሁም ጋዜጠኛ አስማመው ሃይለጊዬርጊስ በተመሳሳይ ሀሳቡን ለመግለጽ ጠይቀው ተከልክለዋል፡፡ ጦማሪ ናትናኤል ፍርድ ቤቱ ሳይፈቅድለት ተናግሯል ወደጎንም ዞሮ አውርቷል በማለት ፍርድ ቤቱ ለጥያቄ አንዲነሳ ሲታዘዝ የናትናኤል ጥያቄ የሁላችንም ጥያቄ ነው በማለት ሁሉም ተከሰሶች አብረውት ተነስተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ሎሎቹ ተከሳሾ አንዲቀመጡ ቢያሳስብም አንቀመጥም በማለት አብረውት ቆመዋል፡፡
ናትናኤል መናገር ሲከለከል ‹‹ከአሁን በፊትም ሀሳባችን እንዳንገልጽ ገደብ ባደረጉብን ዳኛ ላይ አቤቱታ ማሰማታችን ይታወሳል፡፡ ህገ መንገስታዊ መብታችንን አክብሩ...ሀሳባችንን እንግለጽ›› ሲል ተናግሯል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ንግግሩን አስቁሞ በመሐል ዳኛው አማካኝነት ‹‹ወዳልሆነ ነገር አታስገቡን›› ሲል ዛቻ መሰል ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
በዚህ ያላበቃው የተከሳሾችና የፍርድ ቤቱ ውዝግብ ጦማሪ አቤል አሁንም ለመናገር አድሉ አንዲሰየው ሲጠይቅ " ስነስርአት ያዙ " በማለት ፍርድ ቤቱ በመከልከሉ ጦማሪ አቤል " እኛ ብቻ ሳንሆን ራሳችሁም ስነስርአት አድርጉ ጥያቄ አለን ሰምታችሁ ምላሽ ስጡን" በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ይህንን ምላሹን ፍርድ ቤቱ ችሎት መድፈር ነው ብሎታል፡፡ ይህንን ተከትሎ ጠበቆች ጣልቃ በመግባት ደንበኞቻቸው አንዲደመጡ ፍርድ ቤቱን በማሳሰብ አቤልም ይህን እድል በመነፈጉ በስሜታዊነት የተናገረው በመሆኑ በተግሳጽ አንዲታለፍ ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ አቤልን በዚህ የጠበቃው ሃሳብ ይስማማ እነደሆነ ሲጠየቅ የጠየቁት መብቴን ነው የምጠይቀው ይቅርታ የለም በማለቱ የችሎት መድፈሩን አስመልክቶ ውሳኔ ለመስጠት ለግንቦት 25 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ይህንን ተከትሎ የአቤል ሀሳብ የሁላችንም ሃሳብ ስለሆነ ሁላችነም በዚያ ቀን ልንቀርብ ይገባል የሚል አቤቱታ ሁሉም ተከሳሾች ቢያሰሙም ፍርድ ቤቱ ፓሊስን አንዲያስወጣቸው በመታዘዙ ችሎቱ ወጥተዋል፡፡ በኋላ ከተከሳሾች ጠበቆች አንደገለጹት የጦማሪ አቤል ጥያቄ አንደኛ ተከሳሽ ሶልያና ሽመልስ ላይ የሚቀርበው የተባለውን የዶክመንተሪ ማስረጃ ሎሎች ተከሳሾችም አንዲያዩት ለመጠየቅ ነበር ፡፡
የዞን 9 ማስታወሻ
1. ዘግይቶም ቢሆን የተወሰደውን የፍርድ ቤቱን የሲዲ ማስረጃዎቸን መሰረዝ አንዲሁም ለአቃቤ ህግ ተጨማሪ ጊዜ አለመስጠት ውሳኔ እናበረታታለን ፡፡ ይህ ውሳኔ ከሶስት ቀጠሮ አስቀድሞ መወሰድና የጓደኞቻችን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት ሊከበር ቢገባውም አሁንም ቢሆን ከመቅረት ይሻላል ፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህንን መሳይ ፈጣን ምላሾችን በመስጠት ጓደኞቻችን ጦማርያን እና ጋዜጠኞች መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ ማሰናበት የሚቀጥለው ብይን ሊሆን ይገባል፡፡ ያልተሰራ ወንጀል ምስክርም ሆነ ማስረጃ ለአመታት ቢፈለግም አይገኝለትም ፡፡
2. ፍርድ ቤት ውስጥ ያለውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አሁንም አሳሳቢ ነው ፡፡ ተከሳሾች ሃሳባቸውን አንዲሰጡ መፍቀድ አንድ ገለልተኛ ፍርድ ቤት ለተከሳሾች ሊሰጠው የሚገባ መሰረታዊ መብት ሆኖ ሳለ ተከሳሾች ይህንን መብት በተደጋጋሚ መነፈጋቸው ከዚም አልፎ ይህንን መብት በመጠየቃቸው ችሎትን አንደደፈሩ መቆጠሩ በጣም አሳዛኝ ነው፡። የዞን9 ጦማርያን እና ጋዜጠኞች እንኳን አሁን ታስረንና ተሰደን መስዋእትነት እየከፈልንበት እያሉ ቀርቶ ቀድሞም ሃሳብን የነጻነት የመግለጽ መብት የማይቀየር ቋሚ እሴታችን አንደሆነ ይታወቃል፡፡ ፍርድ ቤቶች ይህንን ቀላል መብት መንፈጋቸው ደግሞ የተለመደውን የስራ አስፈጻሚው አካልነታቸው ሃሜት የሚያጠናክር ከመሆን ውጪ ሌላ ፋይዳ የለውም ፡፡
አሁንም ስለሚያገባን እንጦምራለን!
ዞን9
ጋዜጠኛ ኤዶም ካሳዬ እና ጦማሪ ማህሌት ፋንታሁን