Wednesday, February 13, 2013

#Valentine’s Day, #Ethiopia: ኢትዮጵያውያን ፍቅር ያውቃሉ?




‹‹ፍቅር ማወቅ እና አለማወቅ›› የሚባል ነገር አለ? ‹‹ፍቅር ማወቅ›› የሚባል ነገር ካለስ - ኢትዮጵያውያን ፍቅር ያውቃሉ? - የዛሬ የፍቅር (የቫለንታይን) ቀን ጽሑፋችን በዚህ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡

መቃጠር (Dating)

“Dating” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል በአገርኛ አማርኛ እኩያ አንድ ቃል ፍቺ ይገኝለት ከተባለ - መቃጠር - የሚለው ተቀራራቢ ይሆናል፡፡ ሆኖም ‹‹አቃጣሪ›› የሚለው የቆየ ቃል የሚሰጠው አሉታዊ ትርጉም ነው፤ ሁለት ሰዎች መሐል ነገር የሚያመላልስ ማለት ሲሆን በፍቅርም ቢሆን አቃጣሪ የሚለው (በተለይም ከጥንታዊ አመጣጡ አንጻር) ቤተሰቦቻቸው ለመገናኘት ዕድሉን የነፈጓቸውን ተፋቃሪዎች በመሐል እየተመላለሰ የፍቅር መልዕክታቸውን የሚያደርስ የሚል ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ትርጉሙን ቦርቀቅ ስናደርገው ደግሞ ሁለት ሰዎች እንዲፋቀሩ ለማድረግ በመሐላቸው የድለላ ሥራ የሚሠራ - የሚያቃጥር (dating agent) - እስከሚል ትርጉም ሊደርስ ይችላል፡፡

የፈረንጅኛውን ትርጉም ስንወስደው ደግሞ የተለየ እና አዎንታዊ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ዊኪፔዲያ ለምሳሌ ለDating  የሚሰጠው ትርጉም እንዲህ ይተረጎማል ‹‹Dating is a form of courtship consisting of social activities done by two people with the aim of each assessing the other's suitability as a partner in an intimate relationship or as a spouse. While the term has several meanings, it usually refers to the act of meeting and engaging in some mutually agreed upon social activity in public, together, as a couple.…››

ኢትዮጵያ ውስጥ አንዳንድ ዘመነኛ ከተሜዎች ካልሆኑ በስተቀር፣ መግጠም አለመግጠማችንን እናጥና ብለው ተከታታይ ቀጠሮዎች አመቻችተው፣ አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ ቀጠሮ በ‹መቃጠር› የሚጠናኑበት እና የሚወያዩበት መንገድ አለ ለማለት ይከብዳል፡፡ አጋጣሚዎች ፈቅደው ከንፈር ለከንፈር ሲገናኙ በሚጀመር የከንፈር ወዳጅነት ድንገት ወደ‹‹ግንኙነት›› ወይም ዕውቅና ያልተሰጠው ፍቅር (affair) ይገባሉ፡፡

ይህንን የመቃጠር ልምድ ማዳበር የግንኙነት ወቅት ለሚኖሩ ክፍተቶችን ለመቀነስ ይረዳል የሚሉ ልምዱ መዳበሩን የሚያበረታቱ ሲኖሩ በሌላ በኩል ደሞ ከባሕላችን ውጪ የሆነና በእኛ ማኅበረሰባዊ ባህሪ ሊለመድምና ውጤታማ ሊሆን አይችልም በሚል ያጣጥሉታል፡፡

ፍቅረኝነት፣ ፍቅር አገላለገጽ እና “Romance”

ልክ እንደ‹dating› ሁሉ ‹romance› ለሚለው ቃልም ሁነኛ የአገርኛ አማርኛ ትርጉም ማግኘት አይቻልም፡፡ ‹romance› ማለት ፍቅርን መግለጫ መንገድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ጥንዶች ፍቅረኞቻቸውን ለማስደሰት ቢፈልጉም እንኳን ፍቅረኛቸውን ለማስደሰት አቅደው የሚያደርጉበት ልምድ/ባሕል የለም ብሎ መከራከር ይቻላል፡፡ እንዲያውም ብዙዎች የፍቅር አጋራቸውን ‹‹ፍቅረኛዬ›› ነች ብሎ ማለት እያሳፈራቸው፤ በእንግሊዝኛ ‹‹ቦይፍሬንዴ/ገርልፍሬንዴ›› ማለት እየቀናቸው ነው፡፡ ያውም ይህ በከተማ ውስጥ ነው፡፡ በገጠሩ ክፍል በምስጢር ከሚጠበቅ የከንፈር ወዳጅነት ተሻግረው ለትዳር ከበቁ በኋላ ፍቅር የሚገለጸው በቁፍጥንና ነው፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያውያን ብሔሮች እና ባሕሎች ብዙም በማይራራቅ ሁኔታ ባሎች ሚስቶቻቸውን በመቆጣጠር እና በመቆጣት የበላይነታቸውን ከማሳየት በላይ ሌላ ፍቅር የሚገልጹበት መንገድ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ማለት ግን ፍቅር የላቸውም ተብሎ ሊተረጎም አይገባም፤ ፍቅር አላቸው ነገር ግን ፍቅራቸውን የመግለጫ መንገድ/ባሕል/ልምድ ግን የላቸውም፡፡ በተደጋጋሚ ሲገለጽ እንደሚስተዋለው ዱላ የፍቅርና ቅናት መገለጫ እየተባለ ቢነሳ አሁን አሁን ግን ጉዳዩ ወንጀል በመሆኑም ጭምር በጊዜ ሂደት ቢያንስ እንደፍቅር መገለጫነት መቆጠሩ ቀርቶአል፡፡

ማቆላመጥ

አንዱ የኢትዮጵያውያን ፍቅርን የመግለጽ ችግርን የሚያንፀባርቀው ፍቅረኞችን ለማቆላመጥ የምንጠቀምበት ቃላት ማጠር ነው፡፡ ፈረንጆቹ ‹‹honey, sweetie, baby…›› እያሉ የፍቅረኛቸው ስም እስኪረሳቸው ሲያቆለማምጡ የኛዎቹ ግን የፍቅረኛቸውን ስም እንኳ በቁልምጫ መጥራት የሚከብዳቸው ጊዜ ይስተዋላል፡፡ ስንቶች ፍቅረኞቻቸውን ‹‹ማሬ፣ ጣፋጯ፣ ፍቅሬ…›› ብለው በአደባባይ ይጠራሉ? ከጓደኞቻቸው ጋርስ በግልጽ ያስተዋውቃሉ? ብዙ ጊዜ ከወጣቶቹ አንደበት የማትጠፋው ‹‹የኔ ቆንጆ›› የምትል ቃል ራሷ፣ የወል ስም እየሆነች አጠቃቀሟ የምር ይሁን የልምድ ለመለየት ያስቸግራል፡፡


ኩራተኝነት

ኩራተኝነት በኢትዮጵያ ወንዶች ውስጥ የተለየ ለፍቅር የመመረጫ መንገድ ነው፡፡ ሴቶቹም ‹‹ኩራቱ…›› ብለው ያደንቁታል፣ ‹‹ጅንኑ…›› ብለው ይዘፍኑለታል፤ ወንዱም ያንኑ ያጠናክራል፡፡ አለዚያ ወንድ ልጅ ፍቅሩን ብሎ ጠብ እርግፍ ቢል፣ ሌላው ቀርቶ እርሷን ለመርዳት ማጀት ቢገባ ‹‹ኤጭ… እሱ ደግሞ ወንድ ነው እንዴ!? ሴታ፣ ሴት ነገር…›› ተብሎ የወንድነት ማረጋገጫውን ሊነጠቅም ይችላል፤ እሱም አይሞክረውም፡፡ ሴቶቹም ‹‹ኮስታራ ወንድ ይስበኛል›› እያሉ ያበረታታሉ ወንዶቹም ‹‹እንኳን ዘንቦብሽ…›› ዓይነት ብለው ነገሩ እንደነበረ ይቀጥላል፡፡

አበሻ ያልሆኑ ወንዶች፣ ፍቅራቸውን መግለጫ ፅጌረዳ አበባ ይሰጣሉ፣ በየሬስቶራንቱ ወንበር ይስባሉ፣ የወይን ጠጅ ብርጭቆ ይሞላሉ፣ የመኪና በር ይከፍታሉ… ወዘተ፣ ወዘተ… እስኪ ኢትዮጵያዊውን ከተሜ እንመልከተው እና ከፈረንጆቹ ኮርጆም ሆነ በራሱ በኢትዮጵያዊ መንገድ ፍቅሩን የሚገልጽበት የተለየ ልምድ የሚባለው ነገር አለ? ምንድን ነው?

በጨዋ ደንብ መለያየት (Silent breakup)

‹መለያየት› በየትኛውም ዓለም ላሉ ጥንዶች ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ ጥቃት አድራሾች በርካቶች ናቸው፡፡ በምዕራቡ ዓለም ዝነኞች ሲያገቡ ‹‹ብንለያይ የፍቅር ሕይወታችንን እንዳትጽፍበት/ፊበት›› ተባብለው ይፈራረማሉ፡፡ ወጣቷ ዘፋኝ ቴይለር ስዊፍት ለኒውስ ዊክ በሰጠችው ቃለምልልስ ‹‹ፍቅረኞቼ ስንለያይ እባክሽ አትዝፈኚብኝ›› ይሉኛል ብላለች፤ በርግጥ ከጆናስ ብራዘርስ ባንድ ታላቅየው ጋር በነበራት የፍቅር ግንኙነት እና መለያየት ዙሪያ እሷም፣ እነርሱም ዘፍነውባታል፡፡

ለኢትዮጵያውያን ግን መለያየት ከሁሉም የባሰ በጣም ከባድ የቤት ሥራ ነው የሚመስለው፡፡ ምዕራብ አገራት ውስጥ ሳይቀር ሚስቶቻቸውን የገደሉ ኢትዮጵያውያን እና ፍቅረኞቻቸውን የቀጡ ሰዎች ቁጥር ተመሳሳይ በደል ከፈፀሙ የአገራቱ ነዋሪዎች ቁጥር የሚበልጥ ይመስላል - በዜና እንደምንሰማው፡፡ በአገራችንም ከማስፈራራት፣ ማሳደድ እና ጥፊ በተረፈ እስከ ጩቤ መማዘዝና አሲድ መረጫጨት መለያየትን እየተከሉ የሚመጡ ነገሮች ሆነዋል፡፡ እርግጥ ነው እነዚህኞቹ ከቁጥራቸው አንፃር ብዙውን ሊገልፁ ባይችሉም፣ በከፊልም ቢሆን መከሰታቸው አሳፋሪ ነው፡፡

ከዚህ በተረፈ እኛም አገር በመለያየት ዙሪያ ከጓዳ ለሕዝብ የበቁ ብዙ ታሪኮች አሉ፡፡ የዘፋኟ የሃይማኖት ግርማ ባል መጽሐፍ ጽፏል፤ ገጣሚው ኤፍሬም ስዩምም እንዲሁ ‹‹ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር›› በማለት በቀድሞ መድብሉ ያሞገሳትን ‹‹ሶሊያና›› የተባለች ሴት፣ መልሶ ረግሟታል፡፡

ትዕግስት እና መቻቻል የሚባል ነገር - በተራ ጥንዶች መለያየትም ላይ አይስተዋልም፡፡ ጫጫታ ይበዛበታል፤ ወዳጅ ጓደኛ ይነካካበታል፣ ሮሮ እና ብሶት ይስተጋባበታል - እስከድብድብም ሊደርስ ይችላል፡፡ ሴቷም በራስዋ ወንዱም በራሱ ከባቢ የግንኙነቱን ጉድፎች የአጋራቸውን ችግሮች ይናገራሉ፡፡ በጣም የተለየ ሁኔታ ካልተፈጠረ በስተቀር አብዛኛው ግንኙነት ሲጠናቀቅ ለወደፌት ሰላምታ ያህል እንኳን የሚሆን ትእግስት አይቀራቸውም፡፡ ተለያይተው ጓደኛ የሚሆኑ ጥንዶች ከስንት አንድ ናቸው፡፡

የፍቅር ቀንና ፍቅርን ማወቅ

እነዚህን እና የመሳሉትን ተያያዥ ጉዳዮች ስንመለከት ኢትዮጵያውያን የቫላንታይን ቀንን ዓይነት በዓላትን የምናከብርበት የባሕል መቆሚያ ሊያጥረን ይችላል፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን (በተለይ ለዚህ የተፈጠሩ የሚመስሉ ኤፍኤሞች) ስለበዓሉ አከባበር ሲያነሱ መጤ ባሕል ነው፣ የእኛ አይደለም፣ የምዕራባውያን ተጽእኖ ነው የሚሉ ቀላል መከራከሪያዎችን ከማንሳት ውጪ የባሕላችን መሠረታዊያንን እና ልምዳችንን እንዲሁም የፍቅር መግለጫ መንገዶቻችንን ለውይይት አንስተው ግን አይስተዋሉም፡፡

ቀኑን ላለማበላሸት ግንኙነቶች ችግሮቻቸውን ዋጥ የሚያደርጉበት፣ በአቻ ሴቶች መካከል ቀኑን አከባበር አስመልክቶ ውድድር ቢጤ ውስጥ የሚገቡበት፣ አልፎ አልፎም ለቀኑ ሲባል ብቻ ለሰዓታት የሚቆዩ ግንኙነቶች የሚፈጠሩበት የመኝታዎች (የኪራይ) ዋጋ በጣም የሚወደድበት ቀን እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የፍቅረኞች ቀን አከባበር ከሚገባው በላይ አትኩሮትን እየሳበ ነው፡፡ በተለይ ጉዳዩ ‹‹በኤፍኤሞች አየር ሰዓት ማሟያ›› እና ‹‹የኢንተርኔት ትርጉም ማንበቢያ›› ከሆነ ወዲህ ቀላል የማይባል የወጣቱ ክፍል ባይፈልግ እንኳን  ጉዳዩን ከትኩረቱ ማስወገድ እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ይህ የባሕላችን የፍቅርን መግለጫ እጥረት መገለጫ እንዲሁም ሁሉም የሚያከብረው ኢ-ሃይማኖታዊ በዓላት/ፌስቲቫሎች እጥረት ሆኖ ሊቆጠርም ይችላል፡፡

ይህ ቀናት የማክበር ሰበብ ፍለጋ ምናልባትም ከፍቅር ባሕላችን አንጻር ፍቅራችንን የምናከብበት ሌላ ቀን ስለሌለን (ዓመቱን ሙሉ ተኮሳትረን ከርመን) ዕድሉንም የመጠቀም አዝማሚያም ይሆናል፡፡ ፍቅረኞች የፍቅረኞች ቀንን ያክብሩ፡፡ ፍቅርን የመግለጽ ባህልም ያዳብሩ፡፡ አትኩሮቱን ገደብ መስጠት ግን ከሚዲያዎቻችንም ሆነ ከእኛ የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡ ለማይገባቸው ጉዳዮች ከአቅም በላይ አትኩሮት መስጠት በቀኑ ማግስት የምንጋፈጠውን ግላዊም ሆነ ማኅበራዊ እውነታ ካለመቀየሩም በተጨማሪ አትኩሮት የሚገባው ጉዳይ ላይ አትኩሮታችንን በሚገባ እንዳንሰጥ እንዳያግደን ያሰጋል፡፡ ቢያንስ፣ ቢያንስ በዕለቱ ስለፍቅር እና የፍቅር ግንኙነትን ተከትሎ ስለምንተገብራቸው ባሕላዊ ድርጊቶቻችን በጎነት እና መሻሻል ስለሚያስፈልጋቸው ልማዶች እያወጋን ብናሳልፈው፣ ዕለቱ ዋጋ-ቢስ ከመሆን ይተርፋል፡፡
---
ማሳሰቢያ፡- ይህ ጽሑፍ የተጻፈው ስለብዙኃኑ እንጂ ስለአንዳንድ የተለዩ /ወጣ ያሉ/ ኢትዮጵያውያን አይደለም፡፡ አስተያየት ሰጪዎችም ራሳቸውን ሳይሆን ብዙኃኑን እና ባሕሉን እያሰቡ ቢሆን ይመረጣል፡፡

5 comments:

  1. >>መቃጠር (Dating)ማቃጠር የማያውቁትን..መቆጣጠር ያለንን በለው!!
    ፩) በከተሞች ወይመ ቀለም ቆጠር በሆነው ኢትዮጵያዊ ዘንድ ከጎረቤት ወጠት ያጥር ላይ ከንፈር ማናካካት፣አዩኝ? አላዩኝ? ስሜት "የጎረቤት ፍቅር ምንኛ ደግ ነው እንቅቡም ሰፌዱም ተላላኪ ነው"የጉረቤት ልጅ መልክት በመስተላለፍ የሠፈር ጎረምሳ ቅናት ጩኸትና ፉጨት ለከፋው የሚቀልጠው ጊዜ ፈቅዶ እድሉ ለገጠመው... (ለመታያየት) ተቀታጥሮ (ቀነ ቀጠሮ አለን) ሻይ ቡና ልጋብዝሽ..ይባልና አነስ ሲል ጮርናቄ(ፖፖሊኖ)፤አለዚያም ቡና በወተት በሸዋ ዳቦ እያጠቀሱ፣አልፎም ቡና ማኪያቶ በኬክ፣ጠንከርም ያለ ክትፎና ጥብስ ተበልቶ በአቅም ልክ'የሳሪስ ወይንጠጅ' ቸስ የሚደረግበት ዘመንም እንደነበር አንርሳ!።
    -ፍቅረኝነት፣ ፍቅር አገላለገጽ እና “Romance”
    ፪)በገጠሩም እንዲሁ በዓመት በዓሉ፣ በክብረበዓሉ፡ሎሚ መወርወር ጥምቀትና መስቀል ጭፈራ (በዳራት) ወይም በጓደኛና በዘመድ ሠርግ፣እንዲሁም በገበያ መሀል የሚደረገው የዓይን ጥቅሻ(ጠበሳ) (ማሽኮርመም) አለዚያም ሥራው ያውጠው ብሎ ጠለፋ ከእነ ውሃ እንስራዋ የገበያ ዕቃዋን እንደተሸከመች መማረክ የዛሬ ወንጀል የቀድሞው ባሕል አይዘንጋችሁ።
    -ማቆላመጥ..
    ፫) መሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ማንቆለጳጰስ(ማቆላመጥ)አይችልም ያለው ማነው? ከቶ ምን የጎበረበት "ፍቅረኛዬ" ወይም በዚያው ወጥላቃ ቋንቋችሁ (ቦይ ፍንድድ፤ገርል ፍንድድ)ማለት ነው። ወይንስ (አካሌ፣ ሆድዬ ፣ ነፍሴ/ነፍሱ፣ እመቤቴ፣ እናቴ፣ አጋሬ፣የክፉ ቀኔ፣አብሮ አደጌ፣ የሀገሬ ልጅ የወንዜ ይላል ሰው እንደገጠመኙና ፍቅር እነዳጀማመሩ። ለመሆኑ ማር ሀገራቸው የሌለ 'ማሬ' አሉ የመረረው ሁሉ 'ጣፋጬ' ስላለ ከኢትዮጵያዊ/ት በላይ ፍቅር አለ ለምትሉ እየኖርን ለምናውቀው ተውልን ይቺ አጓጉል ውጭ ቃርሚያና ማደባለቅ ሀገርን ባሕልን ይበራዛል ወይም ያጠፋል እንጂ ትውልዱን አያስተምርም በለው!!...

    ***ለመሆኑ ዛሬ የት ነን?
    ዛሬማ ሁሉ ነፃ በሆነት አባት እናት የሀገር ሽማግሌ በተናቀበት ባለቤትና ደባሉ በተመሰቃቀለበት ከደረት ዳንስ ቂጥ ማማታት ተሸጋግረን መን ሰው ብለን ማንን ፈርተን..ዕድሜ አይጠይቅ እውቀትና ቦታ ባሕል የለ ሃይማኖት እንዲሁ ስረት የገቡትም ገብተው ላልገቡትም ሄደንላቸው አልን "ምንድነው ማፈር ?"
    ከእስክስታማ አልፎ መወነጥ፣ ቂጥ ማንቀጥቀጥ፣እንብርት እያሳዩ፣ ውስጥ ልብስ እያረጉ በከተማ መጀረር ፍቅርና 'ዴቲንግ ከሮማ' ተደባልቆ ሮማንዴዲንግ ይሆናል ..አንዳንዴ ሮማውያን??(ወንዱም ሴቱም)ሸዋ እቃህን ሸፍን በለው!!
    -ኩራተኝነት
    ፬) ኩሩ፣ ጅንን፣መልከመልካም፣ሽንቃጣ፣ቁንን፣ቆፍጣና፣ወንዳወንዳ፣ብርት መዝጊያ የሚሆን!ለነገሩ ሕዝቡ በኮንደሚኒየም መኖር ስለጀመረ ኢህአዴግም የራስህ ጣራና ግድግዳ እንጂ መሬት የለህም ሰላለው ያ ዘፈን ላለፈው ትውልድ እንጂ የአሁኑማ ሱሪውን አስተካክሎ ከፍ አድርጎ የማይታጠቅ...እብርትና ጭን አትሸፈን ተብሎ ዝንብ የሚወረው የወንድሙን ጓደኛ የዘመዱን ጓደኛ የሚተኛ ትውልድ ድንቄም ኩራተኛ/?ድሮማ ቃሉማ(ኮራ ተኛ)ነበር ።ጭቅጭቅ የማያውቀው የአራዳ ልጅ !!!
    -በጨዋ ደንብ መለያየት (Silent breakup)
    ፭) በጨዋ 'ደንብ መለያት' መጀመሪያ የትርጓሜ ሥህተት አለ..ሕግና ባሕል፣ወግ አና ሃይማኖት ሲጣረሱ መለያትና መፋታት የተለያየ ትረጓሜና አፈፃጸም እንዳላቸው በተለይ ባሕልና ሃይማኖት በሌላቸው ሀገሮች 'ፍቺ ቀልድ' ሲሆን 'ባህል ወግና ሃይማኖት' ባላቸው ሀገሮች 'ጋብቻ ከብር' ለመሆኑ ያውቃሉን? "ሀብትሽ በሀብቴ፣ ሞት እስኪለየኝ ድረስ በህመም በሀብት እጥረት፣መከነች ብዬ ላልፈታሽ" የሚለውን... ሚስቴ አትበል የአንተ የብቻህ አደለችም(አልገዛሃትም) ንበረቱ እኛ የምንፈቀድልህ ነው !"ፍቅር እስከመቃብር ልከዳሽ ላልከዳሽ" የለም ውሽማ ባለቤት ይሁን በማለት..የውሸት ሳይንስና ፍልስፍና የራሳቸው ባሕልና ወግ ያላቸው "ዶሞክራሲያዊ ፖለቲካ" እየነዙ የገንዘብና የመራጭ ብዛት ማሰባሰቢያ እንደ ኢህአዴግ "አብዮታዊ ዴሞክራሲ" ይሞላፈጣል።"የእኛ "ሃይማኖታዊ ባህልና ወግ' የእነሱ ጠላት የእነሱ "ዴሞክራሲዊና ሳይንሳዊ ፍልስፍና" የእኛ ጠላት ነው "
    *ለዚህም ብዙ ንፁህ የሀገራችን ሰዎች ወገናቸውን ሴት/ወንድ የኑሮና የፍቅር አጋራቸውን ሲደበድቡ ሲገሉ ታያላችሁ!ያሉበት ሀገር ሕጉም የመጣህበት ሀገር ህግ፣ ባህልና ወግ እንደሌለ በመቁጠር የጥቁር ቀለምህን ብቻ በማየት በቲቪ ታሪክህን አቅርበው ያላግጣሉ።በውስጡ ብዙ ተዘርዝሮ የማያልቅ ሸፍጥ አለ።እንዲያው በቀላሉ ወያኔ ከማን? ምን? ነፃ እንደሚወጣ ሳይታወቅ ኢትዮጵያንና ትግራይን ነፃ አወጣለሁ ብሎ ሀገር በቀል ሞልፋጦችም ነገሩ ሳይገባቸው ያንኑ ሲያራግቡ መቀመቅ እንደጨመሩን ሁሉ አሁንም የውጭ ወሬ እንደትልቅ ዕውቀት ይዘው ያራግባሉ !!። ማን የፍቅር ቀንና ፍቅርን ማወቅ ያውራ? የነበረ ማን ያርዳ? የቀበረ!!

    እንደዚሁ ፅሑፍ አቅራቢ ሀተታ የፍቅረኖች ቀን (ኤዩ ቫላንታይንሰ)፭-፩ )"ለቀኑ ሲባል ብቻ ለሰዓታት የሚቆዩ ግንኙነቶች የሚፈጠሩበት የመኝታዎች (የኪራይ) ዋጋ በጣም የሚወደድበት ቀን እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡፭-፪) ይህ የባሕላችን የፍቅርን መግለጫ እጥረት መገለጫ እንዲሁም ሁሉም የሚያከብረው ኢ-ሃይማኖታዊ በዓላት/ፌስቲቫሎች እጥረት ሆኖ ሊቆጠርም ይችላል፡፡፭-፫)ሰበብ ፍለጋ ምናልባትም ከፍቅር ባሕላችን አንጻር ፍቅራችንን የምናከብበት ሌላ ቀን ስለሌለን (ዓመቱን ሙሉ ተኮሳትረን ከርመን) ዕድሉንም የመጠቀም አዝማሚያም ይሆናል፡
    -የፍቅር ቀንና ፍቅርን ማወቅ
    ፮) እንደእኔ ግለሰቡ ሰፊ ልምድ የውጭ ሀገራትን ቋንቋ ባሕል ሃይመኖት ዳሰሳ የምመክረው ቢኖር በውጭው ዓለም ፫፻፷፬ ቀን እናትህ ትበዳ እያለ የሚኖር ልጅ እናት በደስታዋ አጠገቧ ያልነበረ ልጅ፣ እናት በሕመሟ አጠገቧ ሆኖ ውሃ ያላቀመሳት በዓመት አንድ ቀን ወደድኩሽ ብሎ አበባ መግዛት ቅጥፈት ነው። ለሚስቱ ዉሃ ያላቀበለ ከጎረቤቱ የደቀለ፣የሸርሙጣ ቂጥ ዳባሽ፣ በዱቤ መጠጥ ጓደኛ አንበሳባሽ፣ 'የአዩ ቫላንታይን' ቀን አበባ ተሸካሚ ሆደ ጩቤ ትውልድ አድሚ አትቀመጭም አትተኚ የሻልሻል ብትቆሚ!!አጉል ሞልፋጣ፣በልጣጣ፣ሙያ የላት፣ለዛዊ ባሕሪ፤የፌስ ቡክ ተለጣፊ እነደኢህዴግ የሌለሽን አለኝ ብለሽ ጡሩንባ የምትለፊ ፀንተሽ በዓላማሽ ከመቆም በሄድሽበት የምትተኝ እንቀቅልፋም ኢትዮጵያዊ ደም የለሽም ይሻላል ክብርሽን ተብቀሽ በድህነት ብትኖሪ፣ እያለሽ የሌለሽ ሆድ አደር ሥጋ ሻጭ ከሚሉሽ። እኔ ለአቺም ለአንተም ብዬ መከርኳችሁ ከእነግዲህ ሥራችሁ ያውጣችሁ 'አዩ ቫላንታይንስን' ሳይሆን አርባ አራቱ የሀገሬ ታቦቶችን አክብሯቸው እነሱ ፍቅርም ፈውስም አላቸው። በኢትዮጵያ የሚገኙ ቋንቋዎች ባህሎች ሐይማኖቶች ለዚያው ኀብረተሰብ በራሱ ዘይቤና ዕምነት ከማንም በበለጠ መልኩ በጣም እጅግ በጣም ጥሩና የሚወደድ ለመሆኑ አረጋግጣለሁ።
    ውብና ደንቅ ሀገረ ኢትዮጵያ በቋንቋ በሃይማኖት በባህል የሚወዳደራት በፍፁም/በጭራሽ የለም!! ኅብረ ብሔር "ሕብረተሰባዊነት ኢትዮጵያ ለዘለ-ዓለም ፀንቶ ይኑር!። በለው በሀገረ ካናዳ ከምስጋና ጋር

    ReplyDelete
  2. Belew,I really like your comment and you commented on it very well. I share your view and we have to love our " አርባ አራቱ የሀገሬ ታቦቶችን አክብሯቸው እነሱ ፍቅርም ፈውስም አላቸው" that is what we have to do. I do appreciate your comment and I am with you. But unfortunately,almost all of Ethiopians are very poor in mind and take everything as it is whatever their white guys did or does. Poor Ethiopians!!!

    ReplyDelete
  3. በለው እይ ይህን አደንቃለሁ፤ ሁላችንም ቆም ብለን በማሰብ ከሌላው ጠቃሚውን ብቻ አንጥረን በማውጣት ጠቃሚውን ከአገርኛው ጋር በማስማማት የራሳችንን ባሕል የምናገዝፍበት እንዲሆን የሁላችንንም ጥረት ይጠይቃል። አዲሱ ትውልድ ባላወቀውም መውቀስ ስለማይኖርበት በኢትዮጵያዊነት ላይ ተመስርተን ማስተማር ን ለነገ የማንለው ግዳጅ እናድርገው። በለው አሁንም በድጋሚ ላመሰግንህና ላደንቅህ እወዳለሁ።

    ReplyDelete
  4. ከላይ የቀረበው አስተያየቴ ኤዲት ሳይደረግ በድንገት የለጠፍኩት ነውና ይቅርታ። በለው እይታህን አደንቃለሁ፤ ሁላችንም ቆም ብለን በማሰብና ከሌላው ጠቃሚውን ብቻ አንጥረን እያወጣን የሚበጀንን ከአገርኛው ጋር በማስማማት የራሳችንን ባሕል የምናገዝፍበት እንዲሆን የሁላችንንም ጥረት ይጠይቃል። አዲሱን ትውልድ ባላወቀው መወቀስ ስለማይኖርበት በኢትዮጵያዊነት ላይ ተመስርተን ማስተማርን ለነገ የማንለው ግዳጅ በመሆኑ ትኩረት ሰጥተን ለስኬቱ እንረባረብ። ሶልያና ሽመልስ፥ በፈቃዱ ኃይሉና በለው ትኩረት ሰጥታችሁ ላበረከታችሁልን ጽሁፍ ምሥጋናዬ ባላችሁበት ይድረሳችሁ።

    ReplyDelete