Sunday, July 7, 2013

“በስመ ተቃዋሚ ተቃቅፎ መሳሳም” - ለትልቁ ዓላማ?



ከጥቂት ጊዜያት በፌት አንድ የመጽሐፍ ዳሰሳ ዝግጅት ላይ ተገኝቼ ነበር፡፡ መጽሐፉ “ፌኒክሷ ዛሬም፣ ሞታም ታንቀላፋለች” ሲሆን ጸሐፊዋ የቀድሞው የሕወሓት አባልና አመራር የአቶ ገብሩ አስራት ባለቤት ወ/ሮ ውብማር ናቸው፡፡ በዳሰሳው ወቅት በትግል ጊዜ ለምን መጽሐፉ ላይ የተጠቀሱትን ችግሮች እንዳልፈቱ ሲጠየቁ ወይዘሮዋ እንዲህ ብለው መልሰው ነበር፡፡

“ደርግን የሚያህል ጠላት ከፊት ለፊታችን እያለ እንዴት እርስ በርስ በመጣላት ጊዜ እናባክናለን? ነጻ ስንወጣ የሕወሓት ፖሊሲና ፕሮግራም ሁሉንም ነገር ይፈታዋል::” ብለን ተውነው ይላሉ፡፡

በኋላ ላይ ደግሞ ሕወሓትን ስለመለወጥ ሲጠየቁ ‹‹ሕወሓት ከዚህ በኋላ የሚለወጥ ድርጅት አይደለም አርጅቷል፡፡ 40 ዓመት በኋላ የድርጅት ባሕሪይ አይቀየርም›› ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

የትኛው ጠላት? የትኛው ትልቁ ዓላማ?

አሁንም ሕወሓት ሥልጣን ከያዘ ከ20 ዓመት በኋላም ቢሆን የዋናው ጠላት ወይም “ትልቁ ዓላማ” ክርክር እንደ መተባበርያ  እና እነደመቻቻያ ሰበብ እንዲሁም እንደአለመተቺያ ምክንያት ይነሳል፡፡ ተቃዋሚዎች እንዲተባበሩ የሚጠየቁት “ዋናውን  ጠላት” ለማንበርከክ ነው፡፡ የትልቁ ጠላት መኖር አገራዊ የፖለቲካ ክርክራችንንም ሆነ የፓርቲ ፖለቲካችንን የሚበጠብጥ  ትልቅ ችግራችን እየመሰለኝ መጥቷል፡፡ መንግሥት/ገዥው ፓርቲ  የተሰኘውን ይህንን ጠላት ለማባረር በሚደረገው ጥረት ውስጥ ለትልቁ ዓላማ ተብሎ የምናጣቸውን ነገሮች ሳናስተውል የምናልፍበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ምሳሌ እናንሳ ብንል ለትልቁ ዓላማ ሲባል የማይተች ጋዜጠኛ አለን፣ ለትልቁ ዓላማ ሲባል የተቃዋሚ ፓርቲ አይነካም፣ ለትልቁ ዓላማ ሲባል ውስጠ ፓርቲ ልዩነቶች ይታፈናሉ (ሲፈነዱ የሚያመጡት አደጋ መባሱ ላይቀር)፡፡ ለትልቁ ዓላማ ሲባል ሐሳብን በነጻነት መግለጽ መብትን የሚያፍኑ ሌሎች ትንንሽ ጨቋኞችን ማበረታታት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለትልቁ ዓላማ ሰበብ ሲባል ጋዜጠኞች ላይ የጥላቻ ፓሮፖጋንዳ ይነዛል፡፡ ትልቁ ዓላማ ሁላችንም ስህተቶቻችንን የምንሸፍንበት አገራዊ የተቃውሞ ሰበብ ሆኖልናል፡፡

“ትልቁ ዓላማ”ና ትርጉሙ

አብዛኛው ተቃዋሚ ፓርቲዎች/ግለሰቦች  ዓላማቸው ቢጠየቁ  ሃገሪትዋ አሁን ካለችበት ሁኔታ በሁሉም መልኩ ተሻሽላ እንድትገኝ ማድረግ እንደሆነ ቢያንስ በግርድፉ ይናገራሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ አሁን ላለን የፖለቲካዊ ሁኔታ ትኩረት እንሰጣለን የምንል ቡድኖችም ሆነ ግለሰቦች በቋንቋ ብንለያይም፣ ብንጠየቅ የምንናገረው ሐሳብም ከዚህ የተለየ አይሆንም የሚል ግምት አለኝ፡፡ (የገዥው ፓርቲ ደጋፊዎች አሁን ባለችው ኢትዮጵያ እንደሚስማሙና እንደማይመለከታቸው ባስብም ኢሕአዴግም ራሱ በተቃዋሚዎች ቦታ ቢሆን የተሻለ አቅም እንደማይኖረው በመገመት  ይህንን ውይይት ወደራሳቸው ቢተረጉሙት አልጠላም፡፡) ነገር ግን አሁን ያለውን ነባራዊ የፓለቲካ ሁኔታ ከመቀየር ረገድ እየሠራን ነው የሚሉት አካላት ሁሉ የሚስማሙበት የሚመስለው ሌላው ነገር ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት መቀየር የሚለውን አካሄድ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ሠላማዊዎቹንም ነፍጥ ያነሱ ቡድኖችንም የሚያስማማ ሁለተኛው የጋራ ሐሳብ መሆኑ ነው፡፡ እንግዲህ ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ የሚስማሙት ተቃዋሚዎች በተመሳሳይ ሁኔታ መንግሥት ለመቀየር የሚያደርጉትን ጥረት ባለማስተባበር ሲታሙ ኖረዋል፡፡ “ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ” ተብለው ሲተቹ ከርመው ቢተባበሩም ደግሞው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመሰባበር አላመለጡም፡፡

እኔ እንዳስተዋልኩት ተቃውሞው ጎራ ያሉ አብዛኛው  ቡድኖች ከሚስማሙባቸው  ጉዳዮች አንዱ መንግሥት ማንኛውንም ተቃራኒ ድምፅ ለማፈን ጥረት ማድረጉን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ይህንን ስርዓት ለመቀየር (ትልቁ ዓላማ) ሲባል እርስበርስ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን  መተው/ማለፍ እንደሚገባ ነው፡፡ ይህ ያልተጻፈ የመግባቢያ ሐሳብ በሕዝቡም በፓርቲዎችም በግለሰቦችም ውስጥ ሰርፆ በተቃውሞ ቡድኖች መካከል ልዩነቶች በተፈጠሩ ቁጥር ሕዝቡንም የሚያስከፋው “እነዚህ እርስ በርስ መስማማት ያልቻሉ እንዴት ነገ መንግሥት ይሆናሉ?” “ እንዴት በዚህ ጊዜ እንኳን ለትልቁ ዓላማቸው ሲሉ ችግሮቻቸውን አያመቻምቹም?” የሚሉት ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ጉዳዩን ከላይ ከላይ ያየነው እንደሆነ የሚረባ ጠንካራ ፓርቲ አለማግኘት የማንኛውም ሕዝብ የተስፋ መቁረጥ ምንጭ ሊሆንበት ይችላል፡፡ ስለዚህ ጠንካራ ፓርቲዎችን ለማየት መመኘትና ደካማ የሚያስመስሉ ችግሮችን መሸሽም ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን መጀመሪያ ትልቁ ዓላማችን አገራችንን ዴሞክራያዊ የተሻለች አገር ማድረግ ነው ወይስ መንግሥትን መቀየር ብቻ? መንግሥትን መቀየር የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት አስፈላጊ ነው ብዬ ባምንም ይህንን የምናደርገው ለወደፊትዋ ዴምክራሲያዊት ኢትዮጵያ የሚስፈልጉ እሴቶችን በመሸርሸር መሆኑ ግን ያሳስበኛል፡፡ ከነዚህ መሸርሸሮች አንዱ ደግሞ ልዩነትን እንደአማራጭ ያለመቀበል አዝማሚያ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ባለን የተዛባ የመቻቻልና ተስፋ ያለማስቆረጥ ጽንሰ ሐሳብ ከቀጠልን እንደአገር በዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ ውስጥ የምናጣው ነገር ከመብዛቱም በተጨማሪ የሚመጣው ስርዓት የተሻለ ለመሆኑ ማረጋገጫ አይኖረንም ብዬ እከራከራለሁ፡፡

መተባበሮች ለምን ይፈርሳሉ?

ለ”ትልቁ ዓላማ” ሲባል ቅድሚያ የሚሰጣቸው የማይመስሉ ነገሮችን መሸፋፈን ባሕላችን እስከዛሬ ውጤታማ ሆኖ አላገኘነውም፡፡ ይህ የአለባብሶ የማረስ ትብብር በአረም ሲያስመልሰን ብዙ ጊዜ አስተውለናል፡፡ እየተሸፋፈኑ የማለፍ ፖለቲካ ከውስጥ ፓርቲ ጀምሮ እስከ አገሪትዋ ወሳኝ የፖለቲካ ጊዜያት ድረስ ብዙ ጊዜ ዋጋ ሲያስከፍለን ቆይቷል፡፡ እነዚህ ያልተተቹ ያልተፈተሹ እርስ በርስ መተባበሮች  መካከል  በተወሰነ መልኩም ቢሆን ለምርጫ 97 ውድቀት አስተዋእፆ ማድረጉ የሚታወስ ነው:: ለ”ትልቁ ዓላማ” ሲባል የሚደረጉ ያልተጠኑ መስማማቶች “ለትልቁ ዓላማ” ሲባል የታለፉ ልዩነቶች ምርጫ 97ትን የሚያህል ስኬት ለማጣት አስተዋ
ፅዖ አድርገዋል፡፡ስለዚህ ለ”ትልቁ ዓላማ” ሲባል የሚታለፉ ልዩነቶቸ መጨረሻውን ውጤት ስኬታማነት ስለሚቀንሱት ለምንድነው የምንተባበረው? ከነማንጋር ነው አብረን መሥራት የምንችለው? የሚለውን ነገር ማጣራትና ልዩነትን በግልጽ ማስቀመጥ ከማይዘልቅ መተባር የተሻለ ለወደፊቱ  ለፓለቲካ ባሕል ጥቅም ይኖረዋል፡፡ አሁን ባለን አካሄድ የመተባበር ሙከራዎቹ ችግሩንም ጭንቀቱንም ከመቀነስ አንጻር የሰጡት ጥቅም አይታየኝም፡፡ እነደውም ደካማ ተስፋ እየሰጡ እርሱንም በአጭሩ እያከሰሙት ብልጭ ድርግም የምትለው የተቃውሞ ፓለቲካ ላይ ተስፋ ለማሳጣት ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡

የምናወርሰው የፖለቲካ ባሕል ምንድነው?

በባሕል ደረጃ ሊገለጽ የሚችል የፖለቲካ ልምድ ባይኖረንም እነደአገር ለምናደርገው የመማር ሒደት መታሰብ ያለበት የምናሳድገውና የምናወርሰው የፖለቲካ ባሕል ምን ይሆናል የሚለውንም ጭምር ነው፡፡ አሁን ባለን ሁኔታ የፖለቲካ ባሕላችን በጠላትና በወዳጅ ልዩነት ብቻ የተወሰነ ሲሆን መሐል ላይ የሚቀመጥ ግራጫ ባሕሪይ የለውም፡፡ ይህ መሐል ያለመቀመጥ ችግር ፖለቲካ ፓርቲዋችን በግድም ቢሆን ወደተለባበሰ መተባበር ሲገፋቸው ይታያል፡፡ ልዮነቶችን የምናተናግድበት መንገድ የንግግር ባሕልን፣ ልዩነትን የማክበርን ሳይሆን ጎራ የመለየትን ከሆነ ለመጪው  ትውልድም ቢሆን የምናወርሰው የፖለቲካ ባሕል ደካማ ይሆናል፡፡

እንደአገር ከ50 ዓመት በፌት የነበሩ ጥያቄዎችን መመለስ ያልቻልን ሕዝቦች ጥያቄዎቹን ለለመለስ የምንጠቀማቸው መንገዶች እንዲህ ደካማ መተባበሮች ላይ የተመሠረቱ ሆነው ከቀጠሉ ችግሮቹን ብቻ ሳይሆን ለመተባበር ሲባል ብቻ የሚነሱ ደካማ ውሕደቶችንም እንደ ባሕል አስተላልፈን ልናልፍ እንቸላለን የሚል ስጋት አለኝ፡፡ እነዚህን ኃላፊነቶች ከግምት ውስጥ ያላስገባ የፓለቲካ ተቃውሞም እስካሁን ውሕደት/አብሮ የመሥራት ችግሮች ምክያትን ሲያጠናም ሆነ ለመፍታት ሲሞክር አይታይም፡፡ የኅብረቶችን መፍረስ በሌላ ኅብረት በመተካት መፍታት የፓለቲካ ባሕሉ ሳይሻሻል እንዲቀጥል ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ጥቃቅን ልምዶችን (መፍረስ መደራጀት) ችላ ማለት የተበላሸና ለማስተካከል ጊዜ የሚፈጅ የፖለቲካ ባሕል ይዘን እንድንቀር እንደማያደርገን  እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡

ለ”ትልቁ ዓላማ “ ሲባል መሰረታዎ እሴቶችን መጨፍለቅ

ልናመጣቸው የምንከራከርላቸው ሰው ልጆች መብት፣ ፍትሕ፣ እኩልነት እሴቶችን ራሳችን ለትልቁ ዓላማ በመቆርቆር ስያሜ እንደረምሳቸዋለን፡፡ ይህንን ለመረዳት ከፖለቲካ ፓርቲ እስከ ሚዲያ ከግለሰብ እስከ ብሎግና ማኅበረሰብ ሚዲያ አይቶ መመስከር ይቻላል፡፡ በዚህ ባህሪያች የተነሳ በየቀኑ የምንጥሳቸው እሴቶች ብዙ ሰዎችን ገፍተው ዓላማ ሲያስቱም አስተውለናል፡፡ (መቼም ትችቴን ተቹብኝ እንደሰበብ ተቀባይነት ባይኖረውም ተፅዕኖውን ዕውቅና መስጠቱ አስፈላጊ ነው) “ትልቁ ዓላማ” የሚባለው ሰበብም የእሴቶች እሴት ሆኖ ሁሉም ንግግር የመብት ጥያቄና ትችት ከሱ በታች ካልሆነ በስተቀር የማናተናግድበት ባሕል ፈጥረንና ብዛኛዎቻችን ተስማምተን ተቀምጠናል፡፡ ምን ነካት/ው? ለዚህ ሲል ምናለ ቢያልፈው? ይሄንን መናገሪያ ጊዜ አሁን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ይነሳሉ፡፡

የአብዛኛዎቹ የዚህ ክርክር ደጋፊዎች የምናስቀድመው “ትልቁን ዓላማ” መሆን አለበት ከማለት በተጨማሪ ጊዜንና ቅድሚያ አሰጣጥን እንደተያያዥ ምክንያች ያነሳሉ፡፡ እነዚህ ምክንያቶች በቂ ሆነው ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት፣ የግለሰቦች መብት በቀላሉ ይጣሳል፡፡ ይህ ባሕል ደግሞ በየቦታው የምናነሳቸውን እሴቶች ተቃራኒ የመሆንን እና ተደራራቢ መመዘኛዎችን የመጠቀም ያጋልጠናል፡፡ የምንቆምላቸው እሴቶች ለእኛ ዓላማ ሲሆን የሚሸረፉ፣ ሌሎች ሲያደርጉት የሚያስወቅሱ ከሆነ ምኑን ቆምንላቸው?

ትንንሽ አምባገነኖች ማሳደግ

ዛሬ ለትልቁ ዓላማ ሲባል ዝምታን የምንመርጥባቸው ጥቃቅን መሳይ ጉዳዮች የምናፈራቸው መሪዎች ላይ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖም መገመት ቀላል ሥራ አይደለም፡፡ ዛሬ እሴቶች እና መርሕዎቸ ሲሸራረፉ ዝም ማለታችን በትንሽ ሥልጣን ትንሽ አምባገነንነትን ሊያበረታታ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ ይህ ትንንሽ አምባገነኖችን የማበረታታት አዝማሚያ ነገ ትልቅ ሥልጣን ላይ ትልቅ አማባገነንነት ላለመፍጠሩ ምንም ማረጋገጫ የለም፡፡ የአመራር ብቃትና ባሕርይ ማጣት ችግር በሰፊው የሚታይበት የተቃውሞ ፓለቲካ ከገዥው ፓርቲ ከሚደርስበት ጫና በተጨማሪ የሚጋፉት ችግሮች አንዱ አመራሩ አለመገራቱ እና  በገዥው ፓርቲ ስም ለስህተቶችቹ  በቀላሉ የማርያም መንገድ ማግኘቱ ነው፡፡ ለ”ትልቁ ዓላማ” ሲባል የምናልፋቸው ስህተቶች ሌላ አምባገነን መሪዎችን መፍጠር አደጋ ውስጥ ገብተን እንዳይሆን አሁንም ቢሆን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የመንግሥት ተቃውሞውን የማዳከም ተፅዕኖ አሳንሶ ማየት አይደለም፡፡ እንደኽዝብ የምንፈልገውን በግልጽ ማወቅና ለዚያ መሽራትና መኖርንና መለማመድ እንደአንድ የክርክር ሐሳብ ለማቅረብ ብቻ ነው፡፡ ለ”ትልቁ ዓላማ” የሚደረጉ ማመቻመቾችም የት ድረስ መሄድ አለባቸው?  የምናጥፋቸውና የማናጥፋቸው መርሕዎች የትኞቹ ናቸው?  የትኛው ላይስ ማስተካከያ መውሰድ ይገባናል? የሚለውን ለመለየትና ከአሁኑ እርምጃ መውሰድ ካልቻልን “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” የሚለው የአበው ምሳሌ እንዳይደርስብን ከመጨነቅ የመነጨ ነው፡፡ የሐሳብ ልዩነታቸውን ተከትሎ ብቻ “ትልቁ ዓላማ” አልተከተላችሁም በሚል ሰበብ ያጣናቸውና የምናጣቸውን ሰዎችም እያሰብኩ እንደጻፍኩት ይታሰብልኝ፡፡

ማስታወሻ፡- “ትልቁ ዓላማ”- The bigger picture የሚለውን የእንግዘኛ ቃል ተክቶ የገባ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment